Great Ethiopian Run (ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ)
6.21K subscribers
2.5K photos
190 videos
6 files
279 links
Official Great Ethiopian Run Telegram Channel.

Call 0116635757 for more details.
Download Telegram
አትሌት ማሞ ሐጫሉ እና ማህሌት ካሳሁን የ2018 ኢትዮ ቴሌኮም ታላቁ ሩጫ በቦቆጂ ሩጫን አሸነፉ

ለአምስተኛ ጊዜ በተደረገውና 12ኪ.ሜ. በሸፈነው የ2018 ኢትዮ ቴሌኮም ታላቁ የቦቆጂ ሩጫ የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን አትሌት የሆነው ማሞ ሐጫሉ ውድድሩን በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ አማን ቃዲ እና አልዬ ቃሲም ተከታትለው የ2ኛ እና 3ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቅቀዋል።

በሴቶች አሸናፊ የሆነችው የአሰላ አትሌቲክስ ክለብ አትሌቷ ማህሌት ካሳሁን ስትሆን፤ ኪያ ፍስሃ ከአሰላ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ሁለተኛ፣ ድርቤ ኢርኮ ሶስተኛ በመሆን አሸናፊዎች ሆነዋል።

የዘንድሮው ውድድር የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ መኪዩ ሙሐመድ ፣ የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር)፣ የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሮዛ ቢያ እና የቦቆጂ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ ብርሃኔ ነገሰ‘ን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ኃላፊዎች እንዲሁም የቦቆጂ ከተማ ነዋሪዎች የተገኙበት ነበር።

የ'ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ’ ተከታታይ ውድድር አራተኛ መዳረሻ የሆነችውና አትሌቶችን በመፍጠር በምትታወቀው ቦቆጂ፤ ዛሬ መነሻና መድረሻውን በቦቆጂ ስታድየም በማድረግ የ15ዓመት በታች የታዳጊዎች ሻምፕዮና ሲካሔድ አባይ ከተማ በሴቶች እንዲሁም ካሊድ ሱልጣን በወንዶች አሸናፊ በመሆን ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በአርሲ አባቶች እና በኢትዮዽያ ብሔራዊ ህዝብ መዝሙር የተጀመረው የዛሬው ውድድር ከአትሌቶች ጠንካራ ፉክክር 2500 የቦቆጂ እና አካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም ከ70 በላይ ሯጮች ከአዲስ አበባ ተጉዘው ተሳትፈውበታል። በተጨማሪም የ11 ዓመት በታች እና የህጻናት ውድድሮችም የዝግጅቱ ተጨማሪ ውበት ነበሩ።

የ'ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ’ የስድስት ተከታታይ ከተሞች ውድድር በቀጣይ መዳረሻው አርባምንጭ ከተማ ሰኔ 21 ቀን 2018 ዓ.ም. ፤ እንዲሁም ሐምሌ 12 በታሪካዊቷ ሐረር ከተማ ላይ ማጠቃለያውን ያደርጋል።
❤7
🤩ሰኔ 21 በአረንጓዴዋ አርባ ምንጭ 10ኪ.ሜ. ሮጠን፣ ሰኔ 27 እንጦጦ ፓርክ ላይ 5ኪ.ሜ. ዱብ ዱብ እንልና፣ ሐምሌ 12 ሐረር ላይ የልወቅሽ ኢትዮጵያ ጉዟችንን እናጠናቅቃለን።🤩

💫ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ💫

✨ይጎብኙ፣ ይሩጡ፣ ሀገርዎን ይወቁ ✨

#GreatEthiopianRun #DiscoverEthiopiaClassics #Arbaminch #EntotoParkCBERun #Harar
❤10
የሶስተኛው አመት የሳፋሪኮም ታላቁ ሩጫ በአርባ ምንጭ የአካባቢ ጥበቃ መልዕክትን በመያዝ የፊታችን እሁድ ይካሔዳል

በጉጉት የሚጠበቀው የ2018 ሳፋሪኮም ታላቁ ሩጫ በአርባ ምንጭ ለሶስተኛ ተከታታይ አመት በመጪው እሁድ ሰኔ 21 ቀን 2018ዓ.ም. በአርባ ምንጭ ከተማ ይካሄዳል። እስካሁን 4 ከተማዎች ላይ ውድድር የተደረገበት የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ (Discover Ethiopia Classics) የስድስት ከተሞች ውድድር አካል የሆነው ይህ የአርባ ምንጭ ውድድር ፤ ዘንድሮም ከስፖርታዊ ይዘቱ ባለፈ የአካባቢ ጥበቃ መልዕክት ላይ ትኩረቱን አድርጓል።

ዘንድሮ ውድድሩ ከፍተኛ ሀገራዊ እና ክልላዊ ትኩረትን የሳበ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ እና አካባቢዋ የሚጓዙ የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ 120 የሚጠጋ ሲሆን፣ ከአርባ ምንጭና አካባቢዋ ደግሞ ቁጥራቸው 2,500 አዋቂዎች እና 500 ህፃናት እና ታዳጊዎች በዚህ ደማቅ የሩጫ ውድድር ላይ ይሳተፋሉ።

የ2018 ሳፋሪኮም ታላቁ ሩጫ በአርባ ምንጭ ከጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር (GIZ) ጋር በመተባበር “ጤናማ መልክዓ ምድር፣ ለጤናማ ህይወት” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ሲሆን፣ አላማውም የመሬት መራቆት የሚያስከትለውን ጉዳት በማስገንዘብ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ጠንካራ ማህበረሰብ ለመገንባት መሟገት ነው። ይህ መሪ ቃል የመሬት ጤንነት ከህዝብ ጤና እና ደህንነት ጋር በቅርብ የተቆራኘ መሆኑን ለማስገንዘብ የተዘጋጀ ነው።

በቅርቡ በደቡብ ኢትዮጵያ የተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ፣ የተፈጥሮ አካባቢያችንን መንከባከብ ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን የሚያስታውስ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። ኮረብታዎች እፅዋቶቻቸውን ሲያጡ እና መሬት ሲጎሳቆል፣ ማህበረሰቦች እንደ መሬት መንሸራተት፣ ጎርፍ እና ድርቅ ላሉ አደጋዎች ይበልጥ ተጋላጭ ይሆናሉ። ስለዚህም ዛፎች፣ ደኖች፣ የሳር መሬቶች እና በጥሩ ሁኔታ የተያዙ የእርሻ ቦታዎች አፈርን በቦታው አጥብቀው በመያዝና የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ እንዲሁም የውሃ አቅርቦትን በማሻሻል የተፈጥሮ አደጋዎችን ስጋት እንደሚቀንሱ ይታወቃል።

በአርባ ምንጭ በጋራ በመሮጥ፣ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ውበት ስለመጠበቅ በጋራ የሚመከርበት ውድድር ይሆናል። እያንዳንዱ እርምጃ መሬትን መንከባከብ ማለት ማህበረሰብን መንከባከብ መሆኑን የሚዘክርም ይሆናል። ይህ ዝግጅት የጤና ራጮችን፣ የመንግስት ተቋማትን፣ የልማት አጋሮችን እና የአካባቢውን ማህበረሰብ በአንድ የጋራ አላማ ያሰባስባል።

ውድድሩ እሁድ ማለዳ ላይ የሚጀመር ሲሆን፣ በአካባቢው የባህል ሙዚቃዎች፣ የማህበረሰብ ተሳትፎ እና በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ በሚደረጉ ገንቢ ውይይቶች የታጀበ ደማቅ ድባብ ይኖረዋል። 2018 ሳፋሪኮም ታላቁ ሩጫ በአርባ ምንጭ ለከተማው ነዋሪዎች ምዝገባ በኢምፔሳ እና በዳሽን ባንክ እያካሄደ የሚገኝ ሲሆን ተሳታፊዎች ሲመዘገቡም የምዝገባ ዋጋ ላይ ልዩ ቅናሽ ከዳሽን ባንክና ከኤምፔሳ ይበረከትላቸዋል፡፡

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በስያሜ አጋርነት ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር እየሰራ ይገኛል። በተጨማሪም ኤምፔሳ፣ የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር (GIZ)፣ ዳሽን ባንክ፣ ፔፕሲ፣ ፋብ ሳሙና፣ ቶፕ ውኃ፣ ኃይሌ ሪዞርት ፤አፍራን ሆስፒታልና ቻናል ዋን የውድድሩ አጋሮች ናቸው።
❤7
አትሌት እስራኤል አባተ ለተከታታይ ዓመት የሳፉሪኮም ታላቁ ሩጫ በአርባ ምንጭ አሸናፊ ሆነ

2018 ሳፋሪኮም ታላቁ ሩጫ በአርባ ምንጭ በአርንጓዴዋ አርባ ምንጭ ስፖርት፣ ቱሪዝምን እና አካባቢ ጥበቃን በአንድ ላይ በማጣመር በድምቀት ተከናውኗል፡፡ በዝግጅቱ ላይ የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር እንደገና አበበ፣ የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ መስፍን መንዛ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች በዝግጅቱ ላይ ታድመዋል።

ውድድሩ መነሻውን ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሲቀላ አደባባይ በማድረግ ፕሮፌሽናል አትሌቶች እና ከአዲስ አባባ ተጓዥ ተሳታፊዎችን ያካተተ ልዩ የ10 ኪ.ሜ ውድድር የተደረገ ሲሆን የ2017 ውድድር አሸናፊ የነበረው አትሌት እስራኤል አባተ የአንደኛ ደረጃነቱን ሲይዝ ሙሉቀን ታደለ ሁለተኛ እና ሙሉነህ ፍቃዱ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ውድድራቸውን ጨርሰዋል።

በሴት አትሌቶች ውድድር ምንትዋብ ወልዴ ቀዳሚውን ደረጃ ይዛ ስታጠናቅቅ ጠንካራ ፉክክር በተደረገበት የሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ፉክክር ሜሮን አበበ እና ሰላም አበበ ተከታትለው ገብተዋል።
 
በተመሳሳይ ርቀት ውድድራቸውን ያደረጉት የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ ተጓዥ ተሳታፊዎች መሐከል በተካሔደው ውድድር በወንዶች የቦቆጂ አሸናፊው ዮሐንስ አየልኝ ሲያሸንፍ አማን ኃ/ማርያም እና አብዮት ሞገስ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘው ጨርሰዋል። በሴቶች ውድድር ሩት ሙሉጌታ ቀዳሚ ስትሆን የግሌ እሸቱ እና ኬቲ ዱትኮ የሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል።

ከ16 አመት በታች ታዳጊ አትሌቶች የተሳተፉበት የ1.5 ኪ.ሜ. ውድድር እና ከ11 አመት በታች ህጽናት የተሳተፉበት የ1 ኪ.ሜ. ውድድር ሌላው የዕለቱ ድምቀት ነበር፡፡

በጋሞ ዞን በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የመሬት መንሸራተት ትኩረት ለመስጠት እና ግንዛቤን ለማስጨበጥ የጀርመን ተራድኦ ድርጅት (GIZ) ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር “ጤናማ መልክዓምድር - ለጤናማ ህይወት” በሚል መሪ ቃል  በአርባ ምንጭ ጎዳናዎች መልእክት ተስተጋብቷል፡፡

አርባ ምንጭ የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ አምስተኛዋ መዳረሻ ከተማ ስትሆን ዛሬ ከተካሔደው የሩጫ ውድድር ባሻገር ትናንት ወደ ዶርዜ መንደር እና አጆራ ፏፏቴ የተደረገ የእግር ጉዞ፣ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር እንዲሁም በጫሞ ሃይቅ ዳርቻ የተደረገ የራት ዝግጅቶች ነበሩ።

የ2018 ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ የመጨረሻ መዳረሻ ታሪካዊቷ ሐረር ከተማ ስትሆን ውድድሩ በሐምሌ 12 ቀን 2018 ዓ.ም. ይካሔዳል።
 
2018 ሳፋሪኮም ታላቁ ሩጫ በአርባ ምንጭ ውድድር ስኬታማ ይሆን ዘንድ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት በስያሜ አጋርነት ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር እየሰራ ነው። በተጨማሪም ኤምፔሳ፣ የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ጂ አይ ዜድ፣ ዳሽን ባንክ፣ ፔፕሲ፣ ፋብ ሳሙና፣ ቶፕ ውኃ፣ ኃይሌ ሪዞርት፣ አፍራን ሆስፒታል እና ቻናል 1 ቲቪ የውድድሩ አጋሮች ናቸው።
📌 ምዝገባ ተጀምሯል!

በቀላሉ በሲቢኢ ብር ፕላስ በነፃ አሁኑኑ ይመዝገቡ 📲

🗓 የዚህ ወር እንጦጦ ፓርክ ሲቢኢ ሩጫችን ሰኔ 27 ይካሔዳል

እንጦጦ ፓርክ ሲቢኢ ሩጫ✨

ቅዳሜ - ሰኔ 27 ቀን 2018 ዓ.ም. እንገናኝ!

#EntotoParkCBERun #GreatEthiopianRun #EntotoCBERun
❤4
ጋዜጣዊ መግለጫ
 
የአዲስ አበባ ሯጮች በአፍሪካ እምብርት ላይ በሚካሄድ ማራቶን ላይ እንዲሳተፉ ግብዣ ቀረበ

በኢትዮዽያ ሩጫ ከስፖርት በላይ ነው ፤ ሩጫ የሀገር ኩራት፣ የጋራ በዓል፣ የጤና ፣ የህብረተሰብ ትስስር እና የነፍስ ደስታ ነው።

በአፍሪካ ዕምብርቷ ኡጋንዳም ተመሳሳይነት ያለውን ስሜት ለመጋራት፣ ታላቁ ሩጫ በኢትዮዽያ ከተስከር ላይት ሩዌንዞሪ ማራቶን ጋር በመተባበር ለሩጫ ወዳጆች ጥሪን አቅርቧል።

ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ የምስራቅ አፍሪካን ተራራማ መልክዓ ምድር ብቻ ሳይሆን፣ እያንዳንዱን የሩጫ ውድድር ወደ ታላቅ በዓል የመቀየር ተመሳሳይ ባህል አላቸው። ከአዲስ አበባ ለሚሄዱ ሯጮች በካሴሴ የሚስተዋለው የባህል ድባብ፣ ሙዚቃ እና የህዝብ አቀባበል እንደ ቤት እንዲሰማ የሚያደርግ የቅርብነት ስሜት አለው።

በሰኔ 27 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ፣ በእንጦጦ ፓርክ ሲቢኢ ሩጫ ላይ የሚሳተፉ እና ሌሎችም የሩጫ አፍቃሪያን፣ ያንኑ የሩጫ መንፈስ በመያዝ ከሀገር ውጪ በመጓዝ ውድድሩን እንዲቀላቀሉ እንጋብዛለን።

ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ.ም. በኡጋንዳ፣ ካሴሴ ከተማ የሚካሄደው ተስከር ላይት ሩዌንዞሪ ማራቶን፣ ከአዲስ አበባ የባህር ዛፍ ጠረን ካለው ቀዝቃዛ አየር ወደ ሳቫናው ግርማ ሞገስ እና ወደ ሩዌንዞሪ ተራሮች ግርጌ የሚያደርጉት ልዩ የሩጫ ጉዞ ነው። በኢትዮጵያ የክረምቱ ዝናብና ቅዝቃዜ ሲጠነከር፣ በዩጋንዳ ካሴሴ ደግሞ ሞቅ ያለ ፀሐይና የኢኩዌተር መስመር ላይ የሚደረግ ውድድር ይጠብቅዎታል።

የተስከር ላይት ሩዌንዞሪ ማራቶን የዓለም አትሌቲክስ ሌብል (World Athletics Label Road Race) ደረጃ ያለዉ ዉድድር ነዉ። ይህም በአትሌቶች ጥራት እና በአደረጃጀት በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ 200 ውድድሮች አንዱ ያደርገዋል። በውድድሩ ከማራቶን በተጨማሪ በ5 ኪ.ሜ.፣ 10 ኪ.ሜ.፣ እና 21 ኪ.ሜ . (ግማሽ ማራቶን) መሳተፍ ይችላሉ።

የሩጫው መስመር በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ በሆነው የንግስት ኤልሳቤጥ ብሔራዊ ፓርክ ይጀምራል። በከበሮና በሙዚቃ በምትደምቀው የካሴሴ ከተማ መንገዶች አድርጎ፣ በበረዶ በተሸፈኑት የሩዌንዞሪ ተራሮች ግርጌ በሚገኘው አስደናቂው የኪሌምቤ ሸለቆ ይዘልቃል። ማጠናቀቂያው ላይ ሲደርሱ፣ ከኋላዎ የተዘረጋው ግዙፍ የተራራ ሰንሰለት ለእርስዎ የሚሰጠው ስሜት ምን ያህል ድንቅ እንደሆነ በራስዎ ይመሰክራሉ።

እንዴት መመዝገብ ይቻላል?

ይህንን ታላቅ የሩጫ በዓል ለመቀላቀል እና በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ፣ አሁኑኑ ከዚህ በታች በተቀመጠው ድረ-ገጽ አማካኝነት በመግባት መመዝገብ ይችላሉ።

www.rwenzorimarathon.com/register
❤13