Great Ethiopian Run (ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ)
6.22K subscribers
2.5K photos
190 videos
6 files
279 links
Official Great Ethiopian Run Telegram Channel.

Call 0116635757 for more details.
Download Telegram
አትሌት እስራኤል አባተ ለተከታታይ ዓመት የሳፉሪኮም ታላቁ ሩጫ በአርባ ምንጭ አሸናፊ ሆነ

2018 ሳፋሪኮም ታላቁ ሩጫ በአርባ ምንጭ በአርንጓዴዋ አርባ ምንጭ ስፖርት፣ ቱሪዝምን እና አካባቢ ጥበቃን በአንድ ላይ በማጣመር በድምቀት ተከናውኗል፡፡ በዝግጅቱ ላይ የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር እንደገና አበበ፣ የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ መስፍን መንዛ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች በዝግጅቱ ላይ ታድመዋል።

ውድድሩ መነሻውን ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሲቀላ አደባባይ በማድረግ ፕሮፌሽናል አትሌቶች እና ከአዲስ አባባ ተጓዥ ተሳታፊዎችን ያካተተ ልዩ የ10 ኪ.ሜ ውድድር የተደረገ ሲሆን የ2017 ውድድር አሸናፊ የነበረው አትሌት እስራኤል አባተ የአንደኛ ደረጃነቱን ሲይዝ ሙሉቀን ታደለ ሁለተኛ እና ሙሉነህ ፍቃዱ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ውድድራቸውን ጨርሰዋል።

በሴት አትሌቶች ውድድር ምንትዋብ ወልዴ ቀዳሚውን ደረጃ ይዛ ስታጠናቅቅ ጠንካራ ፉክክር በተደረገበት የሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ፉክክር ሜሮን አበበ እና ሰላም አበበ ተከታትለው ገብተዋል።
 
በተመሳሳይ ርቀት ውድድራቸውን ያደረጉት የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ ተጓዥ ተሳታፊዎች መሐከል በተካሔደው ውድድር በወንዶች የቦቆጂ አሸናፊው ዮሐንስ አየልኝ ሲያሸንፍ አማን ኃ/ማርያም እና አብዮት ሞገስ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘው ጨርሰዋል። በሴቶች ውድድር ሩት ሙሉጌታ ቀዳሚ ስትሆን የግሌ እሸቱ እና ኬቲ ዱትኮ የሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል።

ከ16 አመት በታች ታዳጊ አትሌቶች የተሳተፉበት የ1.5 ኪ.ሜ. ውድድር እና ከ11 አመት በታች ህጽናት የተሳተፉበት የ1 ኪ.ሜ. ውድድር ሌላው የዕለቱ ድምቀት ነበር፡፡

በጋሞ ዞን በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የመሬት መንሸራተት ትኩረት ለመስጠት እና ግንዛቤን ለማስጨበጥ የጀርመን ተራድኦ ድርጅት (GIZ) ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር “ጤናማ መልክዓምድር - ለጤናማ ህይወት” በሚል መሪ ቃል  በአርባ ምንጭ ጎዳናዎች መልእክት ተስተጋብቷል፡፡

አርባ ምንጭ የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ አምስተኛዋ መዳረሻ ከተማ ስትሆን ዛሬ ከተካሔደው የሩጫ ውድድር ባሻገር ትናንት ወደ ዶርዜ መንደር እና አጆራ ፏፏቴ የተደረገ የእግር ጉዞ፣ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር እንዲሁም በጫሞ ሃይቅ ዳርቻ የተደረገ የራት ዝግጅቶች ነበሩ።

የ2018 ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ የመጨረሻ መዳረሻ ታሪካዊቷ ሐረር ከተማ ስትሆን ውድድሩ በሐምሌ 12 ቀን 2018 ዓ.ም. ይካሔዳል።
 
2018 ሳፋሪኮም ታላቁ ሩጫ በአርባ ምንጭ ውድድር ስኬታማ ይሆን ዘንድ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት በስያሜ አጋርነት ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር እየሰራ ነው። በተጨማሪም ኤምፔሳ፣ የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ጂ አይ ዜድ፣ ዳሽን ባንክ፣ ፔፕሲ፣ ፋብ ሳሙና፣ ቶፕ ውኃ፣ ኃይሌ ሪዞርት፣ አፍራን ሆስፒታል እና ቻናል 1 ቲቪ የውድድሩ አጋሮች ናቸው።
📌 ምዝገባ ተጀምሯል!

በቀላሉ በሲቢኢ ብር ፕላስ በነፃ አሁኑኑ ይመዝገቡ 📲

🗓 የዚህ ወር እንጦጦ ፓርክ ሲቢኢ ሩጫችን ሰኔ 27 ይካሔዳል

እንጦጦ ፓርክ ሲቢኢ ሩጫ✨

ቅዳሜ - ሰኔ 27 ቀን 2018 ዓ.ም. እንገናኝ!

#EntotoParkCBERun #GreatEthiopianRun #EntotoCBERun
❤4
ጋዜጣዊ መግለጫ
 
የአዲስ አበባ ሯጮች በአፍሪካ እምብርት ላይ በሚካሄድ ማራቶን ላይ እንዲሳተፉ ግብዣ ቀረበ

በኢትዮዽያ ሩጫ ከስፖርት በላይ ነው ፤ ሩጫ የሀገር ኩራት፣ የጋራ በዓል፣ የጤና ፣ የህብረተሰብ ትስስር እና የነፍስ ደስታ ነው።

በአፍሪካ ዕምብርቷ ኡጋንዳም ተመሳሳይነት ያለውን ስሜት ለመጋራት፣ ታላቁ ሩጫ በኢትዮዽያ ከተስከር ላይት ሩዌንዞሪ ማራቶን ጋር በመተባበር ለሩጫ ወዳጆች ጥሪን አቅርቧል።

ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ የምስራቅ አፍሪካን ተራራማ መልክዓ ምድር ብቻ ሳይሆን፣ እያንዳንዱን የሩጫ ውድድር ወደ ታላቅ በዓል የመቀየር ተመሳሳይ ባህል አላቸው። ከአዲስ አበባ ለሚሄዱ ሯጮች በካሴሴ የሚስተዋለው የባህል ድባብ፣ ሙዚቃ እና የህዝብ አቀባበል እንደ ቤት እንዲሰማ የሚያደርግ የቅርብነት ስሜት አለው።

በሰኔ 27 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ፣ በእንጦጦ ፓርክ ሲቢኢ ሩጫ ላይ የሚሳተፉ እና ሌሎችም የሩጫ አፍቃሪያን፣ ያንኑ የሩጫ መንፈስ በመያዝ ከሀገር ውጪ በመጓዝ ውድድሩን እንዲቀላቀሉ እንጋብዛለን።

ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ.ም. በኡጋንዳ፣ ካሴሴ ከተማ የሚካሄደው ተስከር ላይት ሩዌንዞሪ ማራቶን፣ ከአዲስ አበባ የባህር ዛፍ ጠረን ካለው ቀዝቃዛ አየር ወደ ሳቫናው ግርማ ሞገስ እና ወደ ሩዌንዞሪ ተራሮች ግርጌ የሚያደርጉት ልዩ የሩጫ ጉዞ ነው። በኢትዮጵያ የክረምቱ ዝናብና ቅዝቃዜ ሲጠነከር፣ በዩጋንዳ ካሴሴ ደግሞ ሞቅ ያለ ፀሐይና የኢኩዌተር መስመር ላይ የሚደረግ ውድድር ይጠብቅዎታል።

የተስከር ላይት ሩዌንዞሪ ማራቶን የዓለም አትሌቲክስ ሌብል (World Athletics Label Road Race) ደረጃ ያለዉ ዉድድር ነዉ። ይህም በአትሌቶች ጥራት እና በአደረጃጀት በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ 200 ውድድሮች አንዱ ያደርገዋል። በውድድሩ ከማራቶን በተጨማሪ በ5 ኪ.ሜ.፣ 10 ኪ.ሜ.፣ እና 21 ኪ.ሜ . (ግማሽ ማራቶን) መሳተፍ ይችላሉ።

የሩጫው መስመር በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ በሆነው የንግስት ኤልሳቤጥ ብሔራዊ ፓርክ ይጀምራል። በከበሮና በሙዚቃ በምትደምቀው የካሴሴ ከተማ መንገዶች አድርጎ፣ በበረዶ በተሸፈኑት የሩዌንዞሪ ተራሮች ግርጌ በሚገኘው አስደናቂው የኪሌምቤ ሸለቆ ይዘልቃል። ማጠናቀቂያው ላይ ሲደርሱ፣ ከኋላዎ የተዘረጋው ግዙፍ የተራራ ሰንሰለት ለእርስዎ የሚሰጠው ስሜት ምን ያህል ድንቅ እንደሆነ በራስዎ ይመሰክራሉ።

እንዴት መመዝገብ ይቻላል?

ይህንን ታላቅ የሩጫ በዓል ለመቀላቀል እና በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ፣ አሁኑኑ ከዚህ በታች በተቀመጠው ድረ-ገጽ አማካኝነት በመግባት መመዝገብ ይችላሉ።

www.rwenzorimarathon.com/register
❤13
ጋዜጣዊ መግለጫ

የ2018 ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ ውድድር ነገ በሐረር ፍፃሜውን ያገኛል፡፡
 
የ2018 ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ ውድድር የመጨረሻ መዳረሻ የሆነውና ለመጀመሪያ ጊዜ በሐረር ከተማ የሚደረገው የ2018 ኢትዮ ቴሌኮም ታላቁ ሩጫ በሐረር ነገ ጠዋት ይካሔዳል።

ዛሬ ረፋድ በሐረር ኢኮ ቱሪዝም ፓርክ በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተነገረው ውድድሩ ነገ ማለዳ ከ1:00 ሰዓት ጀምሮ መነሻ እና መድረሻውን በዱቅ በር / ሐረር በር ፊት በማድረግ ይከናወናል።
 
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሐረር ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያዘጋጀው ውድድር ከመደበኛው የሩጫ ውድድር ባሻገር ዛሬ ማምሻውን የእግር ጉዞ እና የጀጎል ግንብን ውስጥ የመጎብኘት እንዲሁም በአጠቃላይ የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ ጉዞ ላይ አብረውት ለነበሩ ተሳታፊዎች እና አጋሮች ዕውቅና የሚሰጥባቸው መርኃ-ግብሮችንም ያካተተ መሆኑ ይፋ ተደርጓል፡፡

በመግለጫው የሐረር ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሚ አብዱልዋሲ በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው “ይህ ታላቅ ስፖርታዊ ክንውን ሀገራችንን እና ውብቷን ሐረርን በስፖርት ቱሪዝም (Sports Tourism) ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ትልቅ ፋይዳ አለው። በዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የመጣችሁ ሁሉ ፤ በሐረር ቆይታችሁ የማይረሳ ውብ ጊዜን እንደምታሳልፉ ሙሉ እምነት አለኝ” የሐረርን ዝግጁነት አመላክተዋል።
 
በነገው የሩጫ ውድድር ፕሮፌሽናል አትሌቶችን ጨምሮ ከአዲስ አበባ ወደ ሐረር የመጡ 110 ተሳታፊዎች በ10ኪ.ሜ. ርቀት ይወዳደራሉ፡፡

በተጨማሪም 2500 የሐረር እና አካባቢው ነዋሪዎች በ5ኪ.ሜ. ውድድር ላይ ተሳታፊ ሲሆኑ ለወደፊት ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ታስቦ በሚዘጋጀው የታዳጊዎችና ህፃናት ውድድሮች ላይ 500 ተሳታፊዎች እንደሚወዳደሩ ይጠበቃል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የቱሪዝም ሚኒስቴርን በመወከል ንግግር ያደረጉት አቶ ንጉሴ ክብሩ በበኩላቸው “የዘንድሮውን የዓመቱን የመጨረሻ ማጠቃለያ ውድድር በታሪካዊቷ የሐረር ከተማ ሲደረግ ያለ ምክንያት አይደለም። ሐረር ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦቿን በማስተዋወቅ፣ ከስፖርት ባሻገር ቱሪዝምን ለማሳደግ ከተከናወኑ በርካታ ስራዎች አንጻር በለውጡ ሂደት በሞዴልነት የምትታወቅ ከተማ  በመሆኗ ነው” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
 
ኢትዮ ቴሌኮምን በመወከል ንግግር ያደረጉት የኢትዮ ቴሌኮም የምዕከላዊ ምስራቅ ክልል ዳይሬክተር አቶ ቸሩ ጅማ “በግንባር ቀደምት ከ132 ዓመታት በፊት፤ ከአዲስ አበባ እስከ ሐረር በተዘረጋው ቀጭን ሽቦ በኩል የተገመደው የሐረርና የኢትዮ ቴሌኮም የታሪክ ግንኙነት፤ ዛሬም በረቀቀው ዲጂታል ሞገድ ይበልጡኑ ጠብቋል። የ2018 ኢትዮ ቴሌኮም ታላቁ ሩጫ በሐረር የስያሜ አጋር በመሆኑ ታላቅ ኩራት ይሰማዋል” ብለዋል።
 
ይህን ውድድር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮዽያ ጋር በመሆን በስያሜ አጋርነት አብሮ የሚሰራው ኢትዮ ቴሌኮም ነው። በተጨማሪም የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ዳሽን ባንክ፣ ፔፕሲ፣ ፋብ ሳሙና፣ ቶፕ ውኃ፣ አፍራን ሆስፒታል፣ ቻናል 1 ቲቪ እና የሐረር ቱሪዝም ኮሚሽን የውድድሩ አጋሮች ናቸው።
❤4