Ethiopian Islamic Affairs Supreme Council
11.2K subscribers
6.54K photos
76 videos
20 files
991 links
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት
Download Telegram
ጠቅላይ ምክር ቤቱ ለ1448ቱ የአረህማን እንግዶች የጤና ምርመራ አገልግሎት ከሚሰጡ የጤና ተቋማት ጋር ውል ተፈራረመ።
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
ጥቅምት 9 /2019 ዓ.ል| ጁማደል አወል 8/1448 ዓ.ሒ
بِسْمِ ٱللَّهِ ٱلرَّحْمَٰنِ ٱلرَّحِيمِ
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
አዲስ አበባ |

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለ2019 ዓ.ል (1448 ዓ.ሂ) የሐጅ ተጓዦች የጤና ምርመራ አገልግሎት ከሚሰጡ 29 የህክምና ተቋማት ጋር ውል ተፈራረመ።

የውል ስምምነቱ የአረህማን እንግዶች ወደ ሳውዲ አረቢያ ከማቅናታቸው በፊት አስፈላጊውን የጤና ምርመራ በተቀናጀ መልኩ በጥራት ለማግኘት እንደሚያስችላቸው የጠቅላይ ምክር ቤቱ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የሐጅና ዑምራ ዘርፍ ኅላፊ ዶክተር ሙሀመድ ሷሊህ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ወቅት ተናግረዋል።

ዘርፉ በዚህ ዓመት የሚያቀርበው የሀጅ አገልግሎትና መስተንግዶ "የላቀ አገልግሎት ለሑጃጆች እርካታ!" በሚል መሪ ሀሳብ ተግባራዊ እንደሚደረግ የገለጹት ኅላፊው የጨረታ መስፈርቱን አሟልተው የተመረጡት 29 የህክምና ተቋማት ደረጃውን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት ለሁጃጆች እንደሚሰጡም አክለዋል።

ውል የፈረሙ የጤና ተቋማት አስፈላጊ የህክምና ቁሳቁስና ባለሙያ ያላቸው በመሆኑ የአረህማን እንግዶች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት አግኝተው የጉዞ ብቃት ማረጋገጫ የህክምና የምስክር ወረቀት እንደሚቀበሉም ዶክተር ሙሀመድ ሷሊህ ጨምረው አብራርተዋል።

የሀጅና ዑምራ ዘርፉ የሳዑዲ ዓረቢያ ሐጅ ሚኒስቴር የሚያወጣቸውን መመሪያዎች መሠረት በማድረግ ተገቢ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ ያመላከቱት ኃላፊው በዛሬው ዕለት ውል የተፈራረሙ የጤና ተቋማት በፈረሙት ውል መሰረት ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲውጡም አደራ ብለዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ሀጅ ከማል ሀሩን በበኩላቸው ለሑጃጆች የሚሰጠው የጤና ብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ዲጅታል በመሆኑ አገልግሎቱን የበለጠ ውጤታማ ያደርገዋል ብለዋል።

​የዘንድሮውን የሐጅ ጉዞ ዝግጅት ቀደም ብሎ የጀመረው ሀጅና ዑምራ ዘርፉ ከምግብ፣ ከትራንስፖርት እና ከሆቴል አገልግሎት አቅራቢ ተቋማት ጋር የስራ ውል በመፈራረም አገልግሎቱን ስኬታማ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••
የኢት/እ/ጉ/ጠ ምክር ቤት ሕዝብ ግንኙነት
ይከታተሉን | Follow us፡
ፌስቡክ | Ethiopian Islamic Affairs Supreme Council
ቴሌግራም | t.me/eiasc1
ትዊተር | https://x.com/eiasc1
የ2019 (1448ዓ.ሒ) የሀጅ ምዝገባ ጥቅምት 12/2019 በመላው ሀገሪቱ በቴክኖሎጂ በተደራጁ 33 የሀጅ ምዝገባ ማዕከላት እንደሚጀምር ተገለጸ።
•••••••••••••••••••••••••••••••••
ጥቅምት 12፣ 2019 ዓ.ል| ጁማዱ አል ኡላ 09 1448 ዓ.ሒ
بِسْمِ ٱللَّهِ ٱلرَّحْمَٰنِ ٱلرَّحِيمِ
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
አዲስ አበባ

​የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሐጅና ዑምራ ዘርፍ "የላቀ አገልግሎት ለሐጃጅ እርካታ" በሚል መሪ ሃሳብ የሚያቀርበውን የ2019 (1448 ዓ.ል) የሐጅ ጉዞ የሀጅ አገልግሎት ምዝገባ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

​የዘንድሮው የሀጅ ምዝገባ ሐሙስ ጥቅምት 12/ 2019 ዓ.ል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በተደራጁ 33 የማስተባበሪያ ጣቢያዎች መካሄድ እንደሚጀምር በመግለጫው ተመላክቷል።

የሀጅ ምዝገባው ጥር 10/2019 ዓ.ል እንደሚጠናቀቅ እና አጠቃላይ ክፍያውም 827,000 (ስምት መቶ ሃያ ሰባት ሺህ) ብር እንደሆነ ተገልጿል።

የሐጅ አገልግሎት ዋጋ ተመን የወጪ መጠንን ለመቆጣጠርና ጥራቱን ለማሻሻል የሳዑዲ ዓረቢያ አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶችን በግልጽ ጨረታ በማወዳደር የተሻለ ስራ ስለመሰራቱም በመግለጫው ተመላክቷል።

በመግለጫው መክፈቻ ላይ ንግገር ያደረጉት የጠቅላይ ምክር ቤቱ ​የልማትና ማህበራዊ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሃሚድ ሙሣ የሐጅ አገልግሎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸው ባለፈው ዓመት የተገኘውን የላቀ ውጤት በዚህ ዓመትም አሻሽሎ ለማስቀጠል የዝግጅት ስራዎች ተጠናቀው ምዝገባ መጀመሩን አብስረዋል።

የጠቅላይ ምክር ቤቱ በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የሀጅና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ሙሀመድ ሷሊህ በጋዜጣዊ መግለጫው ዕለት እንዳስረዱት ሀጅና ዑምራ ዘርፉ ባለፈው ዓመት ባስመዘገበው የላቀ አፈጻጸም ከሳዑዲ ዓረቢያ ሐጅ ሚኒስቴር ከፍተኛው የክብር ማዕረግ የሆነውን የለበይቱም የአልማዝ ደረጃ ሽልማት አግኝቷል።

ዶክተር ሙሀመድ ሷሊህ አክለውም በዚህ ዓመትም አገልግሎትና መስተንግዶውን የሳዑዲ ሀጅ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ መሰረት ደረጃውን ጠብቆ እንዲፈጸም ለማድረግ በቂ የዝግጅት ስራ መሰራቱን ጠቅሰው ንያ ያላቸው ሁሉ ከወዲሁ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የሀጅ ምዝገባ ማዕከል እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርበዋል።

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ​የፕሬዝዳንት ዋና ጽህፈት ቤት ዋና ኃላፊ ዑስታዝ አቡበከር አህመድ በበኩላቸው ሐጅ በእስልምና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የአምልኮ ስርዓት በመሆኑ ሀጅ የማድረግ አቅሙ ያላቸው ምእመናን በመዘግየታቸው ምክንያት እድሉን እንዳያጡና በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ጫና እንዳይፈጥሩ በጊዜ እንዲመዘገቡ ጥሪ አድርገዋል።

ጋዜጣዊ መግለጫውን በንባብ ያቀረቡት የጠቅላይ ምክር ቤቱ የአስተዳደር ጉዳዮችና የተቋማዊ ልህቀት ምክትል ፕሬዝዳንት ዑስታዝ ተምኪን አብዱላሂ የሐጅ ምዝገባ የልዩ መስተንግዶ (VIP) እና የትውልደ ኢትዮጵያ (ዲያስፖራ) የሐጅ አገልግሎትን በተመለከተ በቀጣይ ማብራሪያ እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ አባላት፣ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና በርካታ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን መግለጫው በተለያዩ ቋንቋዎች ይፋ ሆኗል።
•••••••••••••••••••••••••••••••••••
የኢት/እ/ጉ/ጠ ምክር ቤት ሕዝብ ግንኙነትና ሚዲያን ይከታተሉ | Follow us፡
ፌስቡክ | Ethiopian Islamic Affairs Supreme Council
ቴሌግራም | t.me/eiasc1
ትዊተር | https://x.com/eiasc1
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ በዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ ሞስኮ አቀኑ።
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
ጥቅምት 13 / 2019 ዓ.ል| ጁማደል አወል 12/1448 ዓ.ሒ
بِسْمِ ٱللَّهِ ٱلرَّحْمَٰنِ ٱلرَّحِيمِ
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
አዲስ አበባ|

የሩሲያ ፌዴሬሽን ሙስሊሞች ሃይማኖታዊ አስተዳደር ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት እና ለኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ ለክቡር ደክተር ሸይኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ በሞስኮ በሚካሄደው ታላቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ በክብር እንግድነት እንዲሳተፉ ይፋዊ ጥሪ አቀርቧል።

​ፕሬዝደንቱ ጥሪ የቀረበላቸው በሩሲያ መዲና ሞስኮ በሚካሄደው ከሩሲያ አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን «በሩሲያ እና በአፍሪካ መካከል ያሉ መንፈሳዊ ድልድዮች ለሰላም እና ለልማት» በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ እንዲሳተፉ ነው።

​ይህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ዋና ትኩረቱ ሰላም፣ ልማትና ደህንነት ሲሆን ከውይይቱ በኋላ በዓለም ዙሪያ ለሚስተዋሉ ግጭቶች የመፍትሄ ሃሳብ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

ጉባኤው የሃይማኖት ተቋማት የጋራ መንፈሳዊና ስነ ምግባራዊ እሴቶች መጎልበት በሚችሉባቸው ነጥቦች ዙሪያ ቀጥተኛና ውጤታማ ውይይት በማድረግ በሩሲያ እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ላለው ሰብአዊ ግንኙነት መጠናከር ምክንያት እንደሚሆኑም በግብዣ ደብዳቤው ላይ ተመላክቷል።

​በዚህ ታላቅ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ከሩሲያ ፌዴሬሽን እና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የሃይማኖት አባቶች እና ታዋቂ ግለሰቦች የሚሳተፉ ሲሆን የክቡር ዶክተር ሸይኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ በጉባዔው ላይ በመገኘት ንግግር በማድረግ የሀገራቸውን መልካም ልምድና ተመክሮ ያካፍላሉ።
••••••••••••••••••••••••••••••••••••
የኢት/እ/ጉ/ጠ ምክር ቤት ሕዝብ ግንኙነት
ይከታተሉን | Follow us፡
ፌስቡክ | Ethiopian Islamic Affairs Supreme Council
ቴሌግራም | t.me/eiasc1
ትዊተር | https://x.com/eiasc1