Addis Ababa Design And Construction Works Bureau
21.5K subscribers
15.3K photos
270 videos
95 files
777 links
Government Organization
Download Telegram
እንኳን ደስ አለን!

ዛሬ በአዲስ አበባ 26 የከተማ አውቶብሶችን ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የመቀየር በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሥራ አስጀምረናል።

ይህ ለሀገራችን የመጀመሪያ የሆነ ታላቅ እርምጃ ሲሆን፣ የትራንስፖርት ወጪንና የአየር ብክለትን ለመቀነስ፣ የዜጎችን ጊዜ ለመቆጠብና የአገር ውስጥ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያግዝ ተጨባጭ የቴክኖሎጂ ሽግግር ነው።

በራሳችን አቅም የተጀመረው ይህ ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል። በቅርቡም 400 አዳዲስ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሠሩ አውቶብሶች ወደ ሀገር ውስጥ ይገባሉ።

ዓላማችን ወጪ ቆጣቢ፣ አካባቢን የሚጠብቅ፣ ፈጣንና ተደራሽ የሕዝብ ትራንስፖርት በመገንባት የዜጎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ ማሻሻል ነው። ለዚህም የትራንስፖርት አገልግሎታችንን የበለጠ ፈጣን፣ ተደራሽና ቀልጣፋ ለማድረግ የጀመርነውን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን።

በራሳችን አቅም፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብን አጠናክረን እንቀጥላለን!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ
❤10👍9
👍11❤6👏2⚡1
እንኳን ደስ አለን! እንኳን ደስ አላችሁ!

አዲስ አበባ በተባበሩት መንግሥታት UN-Habitat በቻይና ያዘጋጀውን የ2026 እ.ኤ.አ የዓለም ከተሞች ቀን “የሸንሃይ አዋርድ” ሽልማት አሸነፈች!!

ይህ ድል ለአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን፣ ለመላው ኢትዮጵያ ታላቅ ኩራት ነው!

በተባበሩት መንግሥታት የሰዎች ሰፈራ ፕሮግራም (UN-Habitat) እና በቻይና ያተዘጋጀውን የሸንሃይ ሽልማት፣ በዘላቂ፣ አካታች፣ ሰው ተኮርና አይበገሬ የከተማ ልማት ውጤታማ ሥራዎችን ላከናወኑ በየዓመቱ ለአምስት ከተሞች የሚሰጥ ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና ነው። በዚህም አዲስ አበባ በ2026 ከተሸላሚ ከተሞች አንዷ ሆናለች።

ይህ ለከተማችን የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አይደለም። በ2024 በUN-Habitat እና በደቡብ ኮሪያዋ ሴኡል ከተማ የተዘጋጀው “የሴኡል ከተማ ሽልማት”አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል።

እነዚህ ተከታታይ ዕውቅናዎች በከተማ ልማት የተከናወኑ ሥራዎችንና የከተማዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያመለክታሉ።

የሸንሃይ ሽልማቱ በተለይም ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑት የከተማ ልማት ሥራዎች ውጤታማነት፣ ዘላቂነትና ለነዋሪዎች ያላቸው ጠቀሜታ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘታቸውን ያሳያል።

ለዚህ ስኬት ካበቋት ዋና ዋና የልማት አቅጣጫዎች መካከል፦

• ሰው ተኮር አቀራረብን ከከተማ መልሶ ማልማት ጋር በማቀናጀት የነዋሪዎችን ፍላጎት ቅድሚያ መስጠት፤

• የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ለማሻሻል የተከናወኑ ሥራዎች፤

• በከተማ ኮሪደሮችና በወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች አካታችና የተቀናጀ ልማትን ማረጋገጥ፤

• የትራንስፖርት አገልግሎትንና ተደራሽነትን ለማሳደግ የተወሰዱ እርምጃዎች፤

• አረንጓዴነትን፣ ጽዳትንና የከተማ ውበትን በማሻሻል ምቹና ለኑሮ ተስማሚ አካባቢ መፍጠር ይገኙበታል።

እነዚህ ተግባራት የከተማዋን እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ ውጤት በመቀየር፣ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት በማሳደግና አዲስ አበባን ተወዳዳሪ ከተማ በማድረግ ረገድ ያላቸውን አስተዋጽኦ ያሳያሉ።

በተለይም በታዳጊ አገራት ከባድ ፈተና የሆነውን የከተማ መልሶ ማልማት በስኬት ማከናወን እንደሚቻል ያሳየችው ተሞክሮ፣ ለሌሎች ከተሞችም ተግባራዊ ትምህርት የሚሰጥ ምሳሌ ሆኗል።

ይህ ድል የተግባር ስኬት፣ የጋራ ጥረትና የጋራ ውጤት ነውና ሁላችንም በድጋሚ እንኳን ደስ አለን!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ
👏20🙏5❤3👍1
አዲስ አበባ በሰው ተኮር ልማቷ በዓለም አቀፍ መድረክ ዳግም ነግሳለች!

አዲስ አበባ ልማቷን ከነዋሪዎቿ ተጠቃሚነት ጋር በማቀናጀት ይህንን እውነታ በተግባር እያሳየች ትገኛለች።

ይህም ጥረት ሌላ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አስገኝቷል። በተባበሩት መንግሥታት የሰው ሰፈራ ፕሮግራም (UN-Habitat) እና በቻይና ትብብር በተዘጋጀው የ2026 የዓለም ከተሞች ቀን ላይ የሸንሃይ ሽልማት ከተቀበሉ ከተሞች መካከል አዲስ አበባ ተካትታለች። ይህ ዕውቅና ከተማዋ በሰው ተኮርና ዘላቂ ልማት የጀመረችውን ጉዞ በተጨባጭ ውጤቶች እያስመሰከረች መሆኗን የሚያሳይ ነው።

የሸንሃይ ሽልማት ዘላቂነትን፣ አካታችነትን፣ ሰው ተኮርነትንና የከተሞችን የተለያዩ ተግዳሮቶች የመቋቋም አቅም በማጎልበት ረገድ ስኬታማ ሥራ ለሚያከናውኑ ከተሞች የሚሰጥ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ነው። ስለሆነም የአዲስ አበባ ተሸላሚነት የከተማዋን ውበትና የተሻሻለ ገጽታ ከማረጋገጥ ባለፈ፣ የልማት ሥራዎቿ በነዋሪዎች ሕይወት፣ በአካባቢ ጥበቃና በከተማዋ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ላይ ያሳደሩትን አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚያመለክት ነው።

ይህ የከተማችን የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አይደለም። በ2024 በUN-Habitat እና በደቡብ ኮሪያዋ ሴኡል ከተማ በተዘጋጀው የሴኡል ከተማ ሽልማት ማግኘቷ ይታወሳል። አሁን የሸንሃይ ሽልማትን ማግኘቷ ደግሞ ይህ ስኬት የአንድ ጊዜ ውጤት ሳይሆን፣ በቀጣይነት በሚመዘገቡ የልማት ውጤቶች ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያሳያል።

ለዚህ ዓለም አቀፍ ዕውቅና መሠረት ከሆኑት ዋና ዋና የልማት አቅጣጫዎች መካከል፦

- ሰው ተኮር የከተማ ልማት፦ የነዋሪዎችን ፍላጎት፣ ደህንነትና የኑሮ ጥራት ማዕከል ያደረገ የከተማ መልሶ ማልማት።

- የመኖሪያ ቤት አቅርቦት፦ ለነዋሪዎች ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ጥራቱ የተረጋገጠና ምቹ የመኖሪያ አማራጭ ለመፍጠር የተከናወኑ ሥራዎች።

- የከተማ ኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት፦ የተፈጥሮ ሀብቶችን ከከተማ ልማት ጋር በማቀናጀት ለመዝናኛ፣ ለማኅበራዊ ትስስር፣ ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና ለአካታች ልማት የሚያገለግሉ አካባቢዎችን መፍጠር።

- ዘመናዊና ተደራሽ ትራንስፖርት፦ የነዋሪዎችን የመንቀሳቀስ አቅም በማሳደግ የተሻሉና ተደራሽ የትራንስፖርት አማራጮችን ማስፋፋት።

- አረንጓዴነትና የአካባቢ ጥበቃ፦ ከተማዋን ንጹሕ፣ ውብ፣ አረንጓዴና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የተከናወኑ የአካባቢ ልማት ሥራዎች።

እነዚህ የልማት አቅጣጫዎች በጋራ የሚያመለክቱት አንድ ዋና መርህ አለ፤ የከተማ ልማት ዋነኛ ዓላማ የሰውን ሕይወት ማሻሻል ነው። መሠረተ ልማት ሲስፋፋ፣ አገልግሎቶች ለሁሉም ተደራሽ ሲሆኑ፣ የኑሮ ምቹነት ሲረጋገጥና የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ሲጎለብት የልማት ትርጉም እውን ይሆናል።

በተለይም በታዳጊ አገራት ከባድ ፈተና የሆነውን የከተማ መልሶ ማልማት የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ሳይጎዳ ማከናወን እንደሚቻል አዲስ አበባ በተግባር እያሳየች ነው። ይህም ለሌሎች ከተሞች የሚጠቀስ ተሞክሮና ከተማን በማልማት ሂደት የሰው ልጅ ክብርና ተጠቃሚነት ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ የሚያስገነዝብ ትምህርት ነው።

ይህ ስኬት የአንድ ተቋም ወይም የአንድ ዘርፍ ውጤት ብቻ አይደለም። የከተማዋን ለውጥ ለማምጣት በጋራ የተጋገዙ የአመራር፣ የባለሙያዎች፣ የሠራተኞችና የነዋሪዎች የጋራ ጥረት ውጤት ነው። ለዚህ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ፣ በትጋት ለሠሩና ድጋፋቸውን ላበረከቱ ሁሉ ከልብ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

አዲስ አበባ ዛሬ የከተማዋን ገጽታ ብቻ አትቀይርም፤ ልማት በሰው ሕይወት ላይ ምን ያህል ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚችልም በተግባር እያሳየች ነው። የሸንሃይ ሽልማትም የዚህ ራዕይና የጋራ ጥረት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ነው።

ይህ ለከተማችን ኩራት፣ ለኢትዮጵያችን ክብር ከመሆኑም ባሻገር፣ የተጀመረውን የልማት ጉዞ በበለጠ ቁርጠኝነት እንድናስቀጥል የሚያነሳሳን ትልቅ ስንቅ ነው!
❤7👍5